Sidebar

ትምህርትና የተማሩ ዜጎች ለኣገር ግንባታ ቍልፍ ሚና ይጫወታሉ። የኢትዮጵያ ዋና ሃብቷ ወጣት ዜጎቿ ናቸው።

ትምህርትና የተማሩ ዜጎች ለኣገር ግንባታ ቍልፍ ሚና ይጫወታሉ። የኢትዮጵያ ዋና ሃብቷ ወጣት ዜጎቿ ናቸው።

ዜጎች ደግሞ የሚገነቡትና ኣገራዊ ማንነት የሚኖራቸው በወላጆች፣ በማኅበረሰቡና በትምህርት ነው። ኢትዮጵያ ኣሁን ያለችበት ኣስቸጋሪ የፖለቲካና የሰላም እጦት ሁኔታ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ነው። ይህም፣ በከፊልም ቢሆን፣ ወጣት ልጆቿ ላይ በትምህርት ፖሊሲውና ኣፈጻጸሙ የተሠራው ብልሹ ሥራ ያስከተለው ውጤት ነው። ወጣቱ ትውልድ ሊያገኝ ይገባው የነበረውን ትምህርትና ኣገራዊ ማንነት እንዲያገኝ ባለመደረጉ ነው። ይህ ኣሁን የደረስንበት የኣገራችን ፖለቲካዊ ችግር በኣንድም ይሁን በሌላ መንገድ የነበረው የትምህርት ሥርዓት ነፀብራቅ ነው።

የኣንድ ኣገር የትምህርት ፖሊሲ የኣገርና የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ሆኖ፣ ለኣገር ኣንድነት ዜጎችን የሚያስተባብር ራዕይ ላይ ያተኮረ መሆን ሲገባው፣ ኢሕኣዴግ በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. ያወጣው ኣጠቃላይ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ከእዚህ ኣንፃር በይዘትም ሆነ በፖሊሲው የተዘጋጀበት መንገድ ብዙ ድክመቶች ነበሩበት። ፖሊሲውም ያለ ሕዝብ ተሳትፎ የወጣ የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ በጥናትና በኣገር ዘላቂ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ኣልነበረም። ባለሙያዎችና ሕዝቡ ሳይወያይበት ተግባራዊ የተደረገው ፖሊሲ በኣገራችን ላይ ብዙ ጉዳት ኣድርሷል።

በቅርቡ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ለኣገሪቱ የትምህርት ችግር መፍትሔ ይሆናል ብሎ “የትምህርትና እድገት ፍኖተ ካርታ” “Ethiopian Education Development Roadmap (2018-30)” ብዙ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና ረዥም ጊዜ የፈጀ ጥናት ኣስጠንቷል። ጥናቱ የትምህርት ሥርዓቱን ችግር ያሳየና ብዙ ጠቃሚ ምክረ-ሓሳብ ያካተተ ነው። ከምክረ-ሓሳቡም ኣንዱ ክፍል ስለ ማስተማሪያ ቋንቋና የኣገር ውስጥ መግባቢያ ቋንቋ የተሰጠው ትኩረት ነው።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ኣንቀጽ 5፣ ቍጥር 2፣ “ዓማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል።” ሲል እንደዚሁም ኣሁንም በትምህርት ሚኒስቴር ድረገጽ ላይ ያለው ኣጠቃላይ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ቍጥር 3.5.4 አማርኛ ቋንቋ ለኣገራዊ ተግባቦት በትምህርት ቤቶች መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል።  [1]   ኣሁንም መንግሥት ያስጠናው ኣዲሱ የትምህርትና እድገት ፍኖተ ካርታ፣ ለኣገራዊ መግባቢያነት ዓማርኛ ከኣንደኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠት እንዳለበት ይገልጻል።

Start Amharic (Federal working language) as a subject from grade 1”.[2]

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትምህርት ሚኒስቴር ከመስከረም ፳፻፲፭ ዓ.ም. ጀምሮ ኣዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እንዳደረገ በመንግሥት ብዙሃን መገናኛ ተናግሯል። ይህም ኣዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ኣካቶታል ከተባሉት ኣዳዲስ ጉዳዮች ውስጥ ኣንዱ ኣገራዊ መግባቢያ ቋንቋን ኣስመልክቶ ተግባራዊ የተደረገው ሥርዓተ-ትምህርት ነው። በእዚህ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም ከኣፍ መፍቻ ቋንቋና እንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ፣ ሊሰጥ ስለሚገባው ኣገራዊ መግባቢያ ቋንቋን ኣስመልክቶ፣ የሚከተለውን ኣስታውቋል፣

“ሦስተኛ ክፍል ላይ ተጨማሪ ቋንቋዎችን መስጠት ይጀመራል፤ በክልሎቹ ውስጥ በስፋት የሚነገረውን ተጨማሪ ቋንቋ በመምረጥ ተማሪዎቹ እንደ ኣንድ የትምህርት ዓይነት እንዲወስዱት ይደረጋል፤”

በዚህ መሠረት፣ ተግባራዊ ሆነ የተባለው ሥርዓተ ትምህርት እንግሊዝኛን በሁሉም የኣገሪቱ ክፍሎች ከኣንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ ኣንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥና ልጆች በኣፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ሲወስን፣ አማርኛን ግን በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች እንደ ኣንድ የትምህርት ዓይነት መሰጠት እንዳለበት ኣይገልጽም። ይህ ተግባር መንግሥት እራሱ ካስጠናውና አማርኛ እንደኣገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንዲሰጥ ከቀረበው ምክረ-ሓሳብ የተለየ ነው። በኦፊሴል ያለውንም የትምህርት ፖሊሲ ይቃረናል፣ የኣገሪቱን የፌደራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አአማርኛን በኣገራዊ መግባቢያ ቋንቋነት እንዲሰጥ ለመደንገግ ያልደፈረ ፖሊሲ ነው። በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን የሥራ ቋንቋ በትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ መንገድ ይከፍታል። ይህም ከመማር ማስተማር ሙያ፣ ከኣገራዊ መግባባትና ኣገር ግንባታ፣ ከኣገራችን የረዥም ጊዜ የዳበር የጽሕፈት ቋንቋ፣ ከኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥቅሙና ከሕዝብ ትስስሩ፣ ከሁሉም በላይ ኣገራችን ኢትዮጵያን በኣንድነትና በነጻነት ከውጭ ከፋፋዮች ከመጠበቅ ኣንጻር ሲታይ፣ በኣገራችን የወደፊት ኣቅጣጫ ላይ ምን ኣንድምታ ይኖረዋል? ይህ ጉዳይ ከተጀመረውስ የኢትዮጵያ ኣገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባር ኣንጻር ምን ኣንድምታ ይኖረዋል? ትምህርት ሚኒስቴር ትኩረቴ ነው ከሚለው የኣገር-በቀል ዕውቀትና፣ የኣገራችንን ቋንቋ ከማበልጸግና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ከማድረግ ኣንጻር እንዴት ይታያል?

ለእዚህ ጉዳይ መፍትሔ መፈለግ ያስችለን ዘንድ P2P እና GESI ”በኢትዮጵያ የጋራ መግባቢያ ቋንቋን የሚያዳብር ርዓተ ትምህርት አስፈላጊነትበሚል ርዕስ በአማርኛ የሚቀርብ ሙያዊ ውይይት ያካሄዳል።

 CLICK HERE TO REGISTER 

December 10, 2022 9 AM EST (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ቅዳሜ ታኅሳስ 1 ቀን ምሽት፣ 11 ሰዓት)

ውይይቱ በሚከተሉት ፍሬ ሓሳቦች ላይ ያተኵራል፤

1.       የኣገራችን የጽሑፍ ቋንቋ ታሪክ እድገትና ለኣገራችን ግንባታ ያደረገው ኣስተዋጽዖ፤

2.      የኣገራችንን የጽሑፍ ቋንቋ የሳይንስና፣ የቴክኖሎጂና የኮምፕዩተር ቋንቋ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች፣ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥረቶችና በኣገራችን ትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ላይ ስለሚኖራቸው አንድምታ፣ እና

3.     ኣገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ከኣገር ኣንድነት፣ ከኢኮኖሚ እድገት፣ ከትምህርት ጥራትና ፋይዳ፣ ከኣገር ደኅንነት ኣንጻር ያለው ሚና፣

ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያካፍሉት ጥናት፣ ወይንም ዕውቀት ካለዎት በሙያዊ ውይይቱ ላይ እንዲያቀርቡ  በትሕትና እንጋብዛለን።  በሙያዊ ውይይቱ ላይ ጥናተዎን ማቅረብ የሚፈልጉ ከሆነና የጥናት ሃሳብዎን ማስገቢያ ፎርም እንድንልክልዎ በ  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. መልዕክት ይላኩልን።

እናመስግናለን!

 

[1] https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20of%20Ethiopia.pdf

[2] https://planipolis.iiep.unesco.org/sites/default/files/ressources/ethiopia_education_development_roadmap_2018-2030.pdf

Deliberate Destruction of Museum, Hospitals, Schools, and Hotels. (2)

Haile Selassie The Pillar of a Modern Ethiopia